post-thumb

ከተዳከመው የንባብ ባህላችን ጀርባ ያሉ እውነታዎች

መንደርደሪያ  

ደራሲ ሌሊሳ ግርማ ለ 20 አመታት ገደማ በስነ ጽሑፍ አለም ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ደማቆቹ የተሰኘ አዲስ የልቦለድ ትርጉም ስራ ያሳተመ ሲሆን 8 መጻሕፍትንም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ ደራሲው በአሁኑ ወቅት ለሕትመት ዝግጁ የሆኑ ስራዎች አሉት፡፡ እዚህን ስራዎች ለገበያ ካበቃ በኃላ፤ ሌሎች አዳዲስ ሥነ-ጽሑፋዊ ስራዎቹን ለህትመት እንደማያዘጋጅ ተናግሯል፡፡

የሙሉ ጊዜ ደራሲ የሆነው ሌሊሳ አሁን ባለው ሁኔታ መጽሐፍ እየጻፉ ማሳተም አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የስነጽሑፍ ስራን ማሳተም፤ ማከፋፈል፤ የወጣበትን ወጪ ማስመለስ ከጊዜ ወደጊዜ አዳጋች አየሆነ መምጣቱን የገለጸው ደራሲው ጽሁፍ መጻፉን ባያቆምም “ስነጽሁፍን እንደ መደበኛ ስራ መስራት” ሊያቆም መሆኑን አስረድቷል፡፡

ሌሊሳ በቅርቡ ከሕትመት ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ የደራሲያን ልፋት እና ውጤት አለመጣጣም እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር፡፡[1] የሥነ ጽሑፍ ብሎም የደራሲዎች መፃኢ እጣ ፈንታ እንደሚያሳስበው በዚሁ ጊዜ የገለጸው ደራሲው “ሥነ ጽሑፍ የተናቀ ነገር መሆኑ ያሳስበኛል፤ ይቆጨኛል’’ ብሏል፡፡

ደራሲ ሌሊሳ ግርማ

ሥነ ጽሑፍ እንደ ሌሎቹ የጥበብ ዘርፎች መጠነኛ ክብር፣ አገልግሎት እና ዋጋ ለምን እንዳላገኘ የሚጠይቀው ሌሊሳ “…ሃያ ዓመት የለፋነው ለምንድነው? ብዬ ራሴን እጠይቀዋለሁኝ…ሥነ ጽሑፍ ከሁሉ የሚያለፋው፣ ከሁሉ የሚያስጨንቀው፣ ከሁሉ ትውልድ የሚያንጸው ሆኖ ሳለ ለምን ከሁሉ የተጨቆነ ሆነ? መቼ ነው ከማስታወቂያ ያለፈ መጽሐፍን ለማስነበብ የጀርባ አጥንት ያለው ሥራ የሚሠራው?...” በማለት ቁጭቱን ገልጿል።

በቅርብ ጊዜአት ፈተና የተደራረበበት የመጻሕፍት ህትመት ዘርፍ

በ2016 ዓ.ም ለመጻሕፍት ህትመት ዘርፍ “ከባድ ዓመት” እንደነበር በመጻሕፍት ንግድና ህትመት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ የሕትመት ግብአቶች ዋጋ መናር፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና በቅርቡ መጻሕፍት ላይ የተጣለው የተጨማሪ አሴት ታክስ ተደራራቢ ፈተናዎችን ይዞ አንደመጣም ይገልጻሉ፡፡

ከውጭ የሚገቡ የወረቀት፣ ቀለም፣ ኮላ እና ተያያዥ የህትመት ግብዓቶች ዋጋ በሸቀጦች የዋጋ ንረት እና በዶላር ጭማሪው ምክንያት እንደናሩ ከ30 ዓመታት በህትመት እና ሽያጭ ላይ የቆዩት አቶ ዓይናለም መዋ ተናግረዋል። በ2 ኪሎ ተኩል ቀለም ላይ ከ400 እስከ 500 ብር ጭማሪ መታየቱንም የሚጠቅሱት አይናለም ከዶላር ጭማሪው በፊት 3ሺ ብር የነበረው አንድ ሪም (እሽግ) ወረቀት 4ሺ ብር እንደገባ ይናገራሉ፡፡ ይህንን ተከትሎም የመጽሐፍት ዋጋ አልቀመስ ብሏል፡፡ 

ወረቀት የመጽሐፍት ህትመት ዋነኛ ግብአት ነው፡፡ የመጽሐፍት ህትመት የሚያገለግሉት ወረቀቶችም የሚገቡት ከውጭ ሀገራት ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የህትመት ወረቀት በሀገር ውስጥ ሊመረት አለመቻሉ ለዘርፉ ፈተና ሆኗል፡፡ ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ በወረቀት ማምረት ስራ ላይ አለመሰማራታቸው ለወረቀት መወደድ በምክንያትነት እንደሚጠቀስ የደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አበረ አዳሙ ይገልጻሉ፡፡

የወረቀት አስመጪዎች በጣም ጥቂት መሆናቸው ለዘርፉ ሌላ ፈተና መሆኑን የሚናገሩት አቶ አበረ፤ ማኅበሩ ከዓመታት በፊት በሰራው ጥናትም ህጋዊ የወረቀት አስመጪዎች ቁጥር 2 ብቻ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ መጽሐፍትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ አካትቷል፡፡

የመጽሐፍት ሕትመት በወረቀት እና ሌሎች ግብአቶች መወደድ እየተፈተነ ባለበት በዚህ ወቅት፤ በሰኔ 27/ 2016 ዓ.ም. ጸድቆ በስራ ላይ የዋለው አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ መጻሕፍትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ አካትቷል፡፡ አዋጁ ከቅዱሳን መጽሐፍት ውጪ ሌሎች መጻሕፍት የተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ እንዲካተቱ ይደነግጋል።

አዋጁ ዘርፉን “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሆን አድርጎታል” ያሉት አቶ አይናለም ከተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁ በኃላ የመጻሕፍ ዋጋ ከ20 እስከ 30 በመቶ እንደጨመረ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ 

ጠበቃ እና የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው መጻሕፍት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ይተቻሉ፡፡[2] “አብርሆት ቤተ-መጻሕፍትን የሚሰራ መንግስት እንዴት ነው በመጽሐፍት ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚጥለው?’’ የሚሉት አቶ ወንድሙ “ይሄ ወደ ፊት እየሄዱ ወደ ኋላ መመለስ ነው’’ በማለት ውሳኔውን ይሞግታሉ፡፡ 

አቶ ወንድሙ ኢብሳ ጠበቃ እና የህግ አማካሪ

ከዚህ ቀደም በ1994 ዓ.ም የወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ወደ አገር የሚገቡና በአገር ውስጥ የሚሸጡ መጸሕፍት እና የታተሙ ጽሑፎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት ከታክስ ነፃ የሚያደርግ ነበር፡፡ አዲሱ አዋጅ ግን ለሃያ ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን ይህንን አዋጅ የሚሽር ነው፡፡  

“የመጽሐፍት ህትመት ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ ነው” ይህንን ሀሳብ የሚሰጡት በእታፍዘር ማተሚያ ቤት የሚሰሩት አቶ አብርሃም አሰፋ ናቸው። ለመጽሐፍት ህትመት ዘርፍ መዳከም “የአሳታሚ ድርጅት አለመኖር፤ የማንበብ ባህል ደካማ መሆን፤ እና የሚታተሙ መጻሕፍት ኮፒ ዝቅተኛ መሆንን” በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታተም አዲስ መጽሐፍ “ብዙ” ከተባለ እስከ 3ሺ ቅጂ ቢታተም ነው፡፡

በቅርብ አመታትም ቢሆን አዳዲስ መጽሐፍት ከሶስት ሺህ ወይ አምስት ሺህ በላይ እንደማይታተሙ የሚገልጹት አቶ አብርሃም በአሁኑ ወቅት የህትመት ዋጋም ከፍ በማለቱ የሚታተሙ መጻሕፍት ቅጂአቸው እየወረደ መምጣቱንና በአሁኑ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታተም አዲስ መጽሐፍ “ብዙ” ከተባለ እስከ 3 ሺ ቅጂ ቢታተም እንደ ሆነ ይገልጻሉ።

የመጽሐፍ ሕትመት ዋጋም በቀደሙት ዓመታት ከነበረው ከ 30 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ እንደታየበት፤ የማሳተም ፍላጎት ያላቸው ደራሲያንም መጨመራቸውንና የአሳታሚ ድርጅት አለመኖር የማሳተም አቅም ያላቸውም ፀሐፊዎች ውስን እንዳደረገው አቶ አብርሃም ይገልጻሉ።

የደራሲያን አበሳ እና የአሳታሚ ድርጅት አለመኖር

በቅርቡ ደማቆቹ የተሰኘውን 8ኛውን መጽሐፍ ለአንባቢያን ያደረሰው ደራሲ ሌሊሳ ግርማ የህትመት ዋጋ አየናረ መምጣቱን ይናገራል፡፡ ሌሊሳ በ2016 ዓ.ም. ሐምሌ ወር 2500 ቅጂ ለማሳተም ያወጣው ወደ 300ሺ ብር ገደማ ነው፡፡ ደራሲው የቀደመ መጻሕፉን በ2500 ቅጂ ለማሳተም ከ 2 አመት በፊት ያወጣው ወጪ ወደ 190ሺ ብር ገደማ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

የመጻሕፍቱን ዋጋ የሚተምነው ደራሲው ቢሆንም አሁን ባለው የህትመት ዋጋ ውድነት አዲስ መጽሐፍ በ400 ወይ 500 ብር ዋጋ ካልተተመነ የወጣበትን ወጪ ለማስመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ሌሊሳ ይገልጻል፡፡ 

ከዛ ባለፈ የመጻሕፍት ስርጭት ችግር መጽሐፍት የወጣባቸውን ወጪ ለማስመለስ እንኳን የማያስችል እንደሆነ የሚገልጸው ሌሊሳ “መጽሐፍት አዟሪዎችም አያዋጣንም ብለው ከዘርፉ እየወጡ በመሆኑ” መጻሕፍትን ማግኘት የሚቻለው  በመደብሮች ብቻ አየሆነ መምጣቱን  ተናግሯል፡፡

አንድ ደራሲ የህትመት ዋጋ በመናሩ ምክንያት የሚያሳትመው ትንሽ ቅጂዎችን ከሆነ የሚያሳትምበት ገንዘብ ከፍ ይላል። በተቃራኒው ከፍ ያለ ቅጂ የሚያሳትም ከሆነ ዝቅ እያለ ይሄዳል። ይሄ የሕትመት ያልተጻፈ ህግ ነው፡፡ የህትመት ዋጋ መናር፤ አሳታሚ አለመኖሩ እንዲሁም የመጻሕፍት ስርጭት እና የክፍፍል ችግር የደራስያን የዘመናት አበሳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ከ4 አመታት በኃላ በቅርቡ አራተኛ እና አምስተኛ መጽሐፏን ለአንባቢያን ያደረሰችው ደራሲ ህይወት እምሻው የመጽሐፍት ሥርጭት እና የክፍፍል ሂደት የዘመናት የደራሲያን ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ትናገራለች፡፡ ደራሲ ገንዘቡን አውጥቶ ካሳተመ በኋላ የሚሄድባቸው አከፋፋዮች ቁጥር ማነስ “የደራሲያንን የድርድር አቅም እየጎዳ” መሆኑን የገለጻችው ህይወት፤ በክፍፍል ሂደቱም “ለደራሲው የማይመቹ ብዙ ችግሮች አሉ” ትላለች።

ደራሲ ህይወት እምሻው

የመጽሐፍት አዟሪዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ መጻሕፍትን ከማዞር ስራ እየወጡ ነው፡፡ ምክንያቱም አዟሪዎች ከስራው ክብደት አንጻር የሚያገኙት ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ እንደሆነ እንደሆነ ይነሳል።

መጽሐፍትን በተገቢው መንገድ ለአንባቢያን ለማቅረብ አዟሪዎች የሚጫወጡት ሚና ትልቅ መሆኑን የምትናገረው ህይወት አዟሪዎች ከዘርፉ አየወጡ በመሆኑ ምክንያት መጽሐፍትን ለመግዛት አስቦበት መደብር የማይሄድ ሰው መጽሐፍትን ማግኘት የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑንና የንግድ ሰንሰለቱም እየተበጠሰ ስለመሆኑም ትገልጻለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዘመናት የደራስያን አበሳ ሆኖ የቀጠለው የደራሲያን አሳታሚ የማጣት ችግር ነው፡፡ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን አንድ ደራሲ ድርሰቱን  የሚያስነብበው በራሱ ገንዘብ አሳትሞ፣ ራሱ አከፋፍሎ፣ የማከፋፈሉን ሥራ ሠርቶ ነበር፡፡ 

ለዘመናት የደራስያን አበሳ ሆኖ የቀጠለው አሳታሚ የማጣት ችግር ነው፡፡

ደራስያኑ የቤት ካርታ ለማተሚያ ቤቱ አስይዘው፣ ወይም ደሞዝተኛ የሆነ ዋስ ጠርተው፣ ወይም ከቤተመንግሥት ሹማምንት ጋር ተወዳጅተው  ወደ ማተሚያ ቤት ዘልቀው መጽሐፎቻቸውን ያስነብቡ እንደነበር አያልነህ ሙላት፤ “ደራስያንን ለማፍራትና ለማበረታታት ምን መደረግ  አለበት?” በሚል ርዕስ በ1985 ዓ.ም በሠሩት ጥናት ጥናት ጠቁመዋል።[3] በዘመነ ደርግ የአሳታሚነት ታሪክ የኢትዮጵያ መጽሐፍት ድርጅት እና ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የብዙ ደራሲያን ስራ ለህዝብ እንዲደርስ በህትመቱ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።[4] 

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ድርጅት ባልደረባ በነበሩት አቶ ተስፋዬ ዳባ የተቋቋመው “የኢትዮጵያ መጽሐፍት ድርጅት” አሳታሚ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የደራስያን ሥራዎች ተቀብሎ ለህትመት አብቅቷል፡፡ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅትም የሶሻሊዝም ርዕዮተ አለምን ከማስተዋወቅ ባለፈ በአሥር ሺህዎች በሚቆጠር ቅጂ እያሳተመ ድርጅቱ ራሱ በመላ ሀገሪቱ በከፍታቸው ከሰላሣ በላይ ቁጥር ባላቸው የመጻሕፍት መደብሮች የኅትመት ውጤቶቹን በማሰራጨት የንባብ ባህል መዳበር ያበረከተው አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነው፡፡

የኢሕአዴግ መንግስት ሲመጣ የኢትዮጵያ መጽሐፍት ድርጅት ከገበያው ሲወጣ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅትም ወደሜጋ አሳታሚነት ተቀየረ። ሜጋ አሳታሚ ለጥቂት ዓመታት የነባርና የአዳዲስ ደራስያን ሥራዎችን ሲያሳትምና ሲያከፋፍል ቆይቶ በትምህርት መርጃ መጽሐፍት፣ በሕጻናት፣ በሙያዊ መጽሐፍትና በመሳሰሉት ላይ ብቻ ትኩረቱን አሳረፈ፡፡

መጽሐፍት አከፋፋዮች መጽሐፉን ለማከፋፈል ከዋጋው ላይ 35 እስከ 40 በመቶ ክፍያ ይቀበላሉ

የአሳታሚ መኖር በረከቱ የተትረፈረፈ እንደሆነ ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ (ዶ/ር) ይገልጻል።[5] ለደራሲው እንቅፋት ከሆኑበት ፈተናዎች መካከል ዋነኛው አሳታሚ ማግኘት ወይም ማሳተሚያ ገንዘብ ፈልጎ ማግኘት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት አንድ ደራሲ ተበድሮ መከራ አይቶ ካሳተመ በኋላ መጻሕፍት አከፋፋዮች መጽሐፉን ለማከፋፈል ከዋጋው ላይ 35 እስከ 40 በመቶ ክፍያ እንደሚቀበሉ የሚናገሩት ደግሞ የደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ አበረ አዳሙ ናቸው። 

ለምሳሌ አንድ ደራሲ አንዱን መጻሕፍ በ400 ብር ዋጋ እንዲሸጥ ዋጋ ካወጣለት፤ ከዋጋው ላይ 40 በመቶውን የሚወስደው አከፋፋዩ ነው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት ከአንዱ መጽሐፍ ላይ አከፋፋዩ 140 ብር የሚወስድ ሲሆን ደራሲው 260 ብር የሚወስድ ይሆናል፡፡

አቶ አበረ አዳሙ የደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት

ይህ ማለት መጽሐፍት አከፋፋዮች ድርሻቸውን የሚያሰሉት ከትርፍ ላይ ሳይሆን ከአጠቃላይ የመጽሐፉ ሽያጭ ላይ ነው። በዚህ ስሌት ደራሲው 260 ብር ቀሪ ቢኖረውም ለማሳተሚያ እስከ 200 ብር ሊያወጣ ይችላል። ታዲያ ደራሲው የሚገኘው ትርፍ በወፍ በረር ስሌት ከ60 እና 70 አይበልጥም ማለት ነው። ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ምረቃና የማስታወቂያ የሚሉትን ወጪዎች ታሳቢ ሳያደርግ ነው።

በዚህም ለደራሲው የሚደርሰው ገንዘብ ልፋቱን ያገናዘበ እንደማይሆን የሚገልፁት አቶ አበረ “የደራሲ መከራ ብዙ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ። ከዛ በተጨማሪ የተወሰኑ አከፋፋዮች ብቻ መጽሐፍትን በካሽ ገንዘብ ገዝተው ለደራሲ እንደሚያከፋፍሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ አከፋፋዮች ደራሲያን ገንዘባቸውን ለመቀበል በማመላለስ ደራሲያንን ማማረራቸው የተለመደ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ 

የንባብ ባህል መዳከም እና የዲጂታል አማራጮች

በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያ መዘመን ምክንያት የህትመት ሚዲያው ለአደጋ በመጋለጡ የንባብ ልምድ መዳከሙን የደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ አበረ አዳሙ ይገልጻሉ፡፡ የንባብ ልምድ አለመዳበር መሰረታዊ ችግር መሆኑን በዚህ ችግር ላይ ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያ መዘመን፤ “ብዙ ሰው ከመጽሐፍ ይልቅ ስልኩን ይዞ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል” ባይ ናቸው። በዚህ ምክንያትም በደርግ ዘመን፣ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመን ከነበረው አንባቢ ይልቅ አሁን እጅግ በጣም የቀነሰ መሆኑን ያነሳሉ።

ማኅበረሰቡ ቀልቡ የተያዘው በስልኩ በሚያገኛቸው ዲጂታል አማራጮች እንደሆነ ደራሲ ህይወት እምሻው ትናገራለች፡፡ “የኢትዮጵያ ህዝብ አያነብም በሚለው ነገር አልስማማም” የምትለው ህይወት ዲጂታል አማራጮች በመጠቀም ተደራሽ መሆን እንደሚያስፈልግ ትናገራለች፡፡ 

ይህንን እድልም በመጠቀም መጽሐፍቶቿንም በትረካ እና በኢ-ቡክ እያደረሰች ትገኛለች፡፡ መጻሕፍትን በዲጂታል አማራጭ ለማቅረብ ያለው ተሳትፎ “አመርቂ እንዳልሆነ” የምትገልፀው ህይወት ደራሲያንም ሥራዎቻቸውን በዚህ መልኩ ለማቅረብ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ትናገራለች። ነገር ግን ጊዜው እየተለወጠ በመሆኑ ከጊዜው ጋር መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ 

ከ150 በላይ መጽሐፍት በተራኪ መተግበሪያ ላይ ቀርበዋል

መጽሐፍትን ተርኮ በማቅረብ የሚታወቀው “ተራኪ” የተሰኘው ኦዲዮ ቡክ እና ፖድካስት ከ150 በላይ መጻሕፍትን በመተረክ በተራኪ መተግበሪያ ላይ እንዳቀረበ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ናሆም ፀጋዬ ይናገራል። መጻሕፍቱ ተተርከው ለገበያ የቀረቡት ከ80 እስከ 150 ብር በሚደርስ ዋጋ ነው፡፡ 

ናሆም ፀጋዬ የተራኪ ዋና ስራ አስፈፃሚ

ለአድማጮች መጻሕፍቱን ለመተረክ ደራሲያን ወጪ እንደማያወጡ እና ሁሉም የፕሮዳክሽን ስራ በድርጅቱ እንደሚከወንና ከደራሲያን ጋር ውል በመፈራረም በአማካይ ከ45 እስከ 50 በመቶ ደራሲያንን ከሥራዎቻቸው ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ አቶ ናሆም ይገልጻል።

ደራሲያን ስራዎቻቸውን ለአድማጮች በትረካ መልክ ለማቅረብ ፍላጎት የላቸውም የሚለው ናሆም ለዚህ ምክንያቱ “ነገሩን ካለመረዳት ነው” የሚል ምልከታ አለው፡፡ 

ይህም ለዘርፉ ፈተና እንደሆነ በመግለጽም መጽሕፍትን በነጻ ማዳመጥ ለለመደ ማኅበረሰብ በክፍያ ማስለመድ አስቸጋሪ መሆኑንም አልደበቀም፡፡ ተራኪ ስራውን ከጀመረ ወደ ከሦስት አመት በላይ ሆኖታል፡፡ በነዚህ አመታት መጻሕፍትን በትረካ ማቅረብ በአጠቃላይ ከአመት አመት እየተሻሻለ፤ ፍላጎቱም እየጨመረ መሆኑን ያስረዳል፡፡ 

ይህ የዲጂታል አማራጭ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለመደ መምጣቱ እንደማይቀር የሚናገረው ናሆም ከባለፈው አመት ጥር ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ በተራኪ መተግበሪያ ላይ ፖድካስትን ጨምሮ የኦዲዮ ቡክን የሚያዳምጡ 234ሺ ተጠቃሚዎችን እንዳፈራ ተናግሯል፡፡ ይህ አሃዝ ከቀደመው አመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን የሚናገረው ናሆም በቀደመው አመት የነበረው የተጠቃሚዎች ቁጥር 104ሺ እንደነበር ጠቅሷል፡፡   

ዘርፉ የተረጋጋ እንዲሆን ምን ምክረ ሀሳብ ቀረበ?

የህትመት ዋጋ መናርን ለመከላከል ወረቀት በሀገር ውስጥ እንዲመረት ጥረት መደረግ እንዳለበት የደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አበረ አዳሙ ሀሳብ ይሰጣሉ። 

መንግስትም ባለሀብቶች በወረቀት ማምረት ዘርፍ እንዲሰማሩ ማበረታቻ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም፤ “ወረቀትም ቢቻል በመንግስት በኩል ወደ ሀገር ውስጥ አየገባ ለትክክለኛ አታሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚከፋፈልበት መንገድ ቢመቻች” የሚል ሀሳብም ያቀርባሉ፡፡ 

“ከመጻሕፍት ውጪ፤ ከእውቀት ውጪ አገርን ለማልማት ደፋ ቀና ማለት የሚታሰብ አይደለም” የሚሉት አቶ አበረ፤ የወጣቱ አእምሮ በንባብ መገንባት እንዳለበት እምነት አላቸው፡፡ “መጽሐፍት እንዲኖሩ፣ በብዛት እንዲታተሙ፣ እንዲሰራጩ ከቀረጥ ነፃ መሆን አለባቸው” ሲሉም አጽአኖት ይሰጣሉ፡፡ 

አቶ አይናለም በበኩላቸው ጠንካራ አሳታሚ ድርጅት ቢኖር ለዘርፉ ጠቃሚ እንደሚሆን ያነሳሉ። የደራሲ ሚና መጻፍ ብቻ መሆን እንሚገባው የሚገልጹት አቶ አይናለም አሳታሚ ድርጅቶች ቢኖሩ ደራሲ መጽሐፍ ጽፎ የአርትኦት፣ የማተም እና የሽያጭ ጣጣ ውስጥ በመግባት አይቸገርም ባይ ናቸው። በዚህ ሂደት ደራሲው ስራውን ለአሳታሚ ድርጅት በማስረከብ የሮያሊቲ ክፍያ ተከፍሎት ወደ ቀጣይ ስራ መሄድ የሚያስችለው መሆኑን ያብራራሉ።

ሥነ-ጹሑፍ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት በድርጅቶች መደገፍና መበረታታት አለበት

በኢትዮጵያ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የቴሌኮም ኩባንያዎች ለመዚቀኞች እና ሌሎች የጥበብ ድጋፍ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት እንደሌላው የጥበብ ዘርፍ ለስነጽሑፍ ሰዎች እና ስራዎች ድጋፍ እንደማያደርጉ ህይወት እምሻው ትናገራለች፡፡ ሥነ-ጹሑፍ እንደ ጥበብ ስራ ተቆጥሮ፤ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት በድርጅቶች መደገፍና መበረታታት እንዳለበት የምትመክረው ህይወት ቢያንስ አቅም ለሌላቸው እና ማሳተም ለማይችሉ ደራሲያን ድጋፍ መደረግ አለበት ስትል ትገልጻለች።

አሁናዊ የመጻሕፍት ዋጋ እና የገበያ ሁኔታ

5 መደብሮችን መሰረት አድርጎ በተሰራው መጠነኛ የዋጋ ጥናት ዳሰሳ፦

 የመጽሐፍ ዋጋ ከቀደመው አመታት ጋር ሲነፃፀር 

ሁለቱ መደብሮች ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ፤

ሁለቱ ደግሞ በመጠኑ መጨመሩን፤ አንድ መደብር ደግሞ መቀነሱን ገልጸዋል።

በ5 መደብሮች በተሰበሰበ መረጃ 

🔵 አዲስ የሚታተም አንድ መጽሐፍ የሚሸጥበት ከፍተኛዋጋ በአማካይ 962 ብር ከ5 ሳንቲም ነው።

🔵 በተመሳሳይ አዲስ የሚታተም አንድ መጽሐፍ የሚሸጥበት ዝቅተኛ ዋጋው በአማካይ 202 ብር ነው።

🔵 በአሁናዊ ገበያ አዲስ የሚወጣ አንድ መጻሕፍ ከጀርባ የሚለጠፈው ከፍተኛ ዋጋው በአማካይ1100 ብር ነው።[6]

🔵 በተመሳሳይ አዲስ የሚወጣ አንድ መጻሕፍ  ከጀርባ የሚለጠፈው ዝቅተኛ ዋጋው 242.5 ብር ነው።

በመደብሮቹ በብዛት የሚስተናገዱት መጽሐፍ ሸማቾች

🔴 4 መደብሮች ወጣቶችን

🔴 2 መደብሮች ጎልማሶችን መርጠዋል።

በብዛት ገዢ ያላቸው የትኞቹ የመጽሐፍት አይነቶች እንደሆኑ ለቀረበ አማራጭ

🔵  የልቦለድ መጻሕፍት በ4 መደብሮች ላይ በብዛት ገዢ አላቸው።

🔵  ሳይኮሎጂ በተመሳሳይ በ4 መደብሮች

🔵  ታሪክ በ 3 መደብሮች  

🔵  ትርጉም በ 2 መደብሮች በብዛት ገዢ አላቸው ።


የግርጌ ማስታወሻ




አልታየህ ኪዳኔ

ጋዜጠኛ

የዚህ ጹሑፍ አዘጋጅ አልታየህ ኪዳኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት የተመረቀ ሲሆን በአሁን ሰዓት በጋዜጠኝነት ሞያ እያገለገለ ይገኛል።

Comments

Leave a Comment

Login or register to interact with an article.